ክቡር አምባሳደር ዶ/ር ሙክታር ከድር በደቡብ አፍሪካ የቻይና ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ከሆኑት Ambassador Chen Xiaodong ጋር የሁለቱን አገራት ትብብርና ግንኙነት ይበልጥ ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።
ክቡር አምባሳደር ዶ/ር ሙክታር ከድር በውይይቱ ወቅት እንዳሉት በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሠረተው የኢትዮጵያ እና የቻይና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በፖለቲካ፣በንግድና ኢንቨስትመንት እና በህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ተጠናክሮ መቀጠሉን አስታውሰዋል።
በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የነበረው ግጭት በሠላም እንዲቋጭ ኢትዮጵያ የወሰደቻቸውን ቁርጠኛ ውሳኔዎች ያብራሩት ክቡር አምባሳደር የተደረሰው የሠላም ሥምምነት ተግባራዊ ለማድረግ እስካሁን በተደረገው እንቅስቃሴ የተገኙ መልካም ውጤቶችን በማውሳት ተግባራዊነቱ ተጠናክሮ መቀጠሉን አብራርተዋል።
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ወደ መገባደድ እየተቃረበ መሆኑን ያስረዱት አምባሳደሩ ከግድቡ ግንባታ ጋር በተያያዘ በታችኛዎቹ የተፋሰሱ አገራት የሚነሱ ጉዳዮችን በአፍሪካ ኀብረት ጥላ ሥር የመርሆዎች ሥምምነት( DoP) መሠረት በሚካሄድ የሶስትዮሽ ድርድር ለመፍታት ኢትዮጵያ ያሳየችውን ቁርጠኝነት አጠናክራ እንደምትቀጥልና ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ ለመስጠት በኀብረቱ በኩል ለሚደረገው ጥረትም ኢትዮጵያ ዋጋ እንደምትሰጥ አረጋግጠዋል።
ሁለቱ ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ በርካታ የጉብኝት፣ የንግድ ልዑካን እና የስራ ልውውጦች ማካሄዳቸውን በተለይም በኢኮኖሚው መስክ በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ትብብር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ መቀጠሉን በማስታወስ ኢትዮጵያ ችግር ባጋጠማት ጊዜ ሁሉ ለተደረገው ድጋፍ በኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ ስም ምስጋና አቅርበዋል።
በደቡብ አፍሪካ የቻይና ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር የሆኑት Ambassador Chen Xiaodong በበኩላቸው ኢትዮጵያ የውስጥ ችግሮቿን በራሷ ጥረት እና በአፍሪካ ህብረት ማዕቀፍ ለመፍታት የምታደርገውን ጥረት ቻይና እንደምታደንቅና እንደምትደግፍ ጠቁመው በታላቁ የህዳሴ ግድብም ቀጠናውን የልማት ትብብር የሚያጠናክር መሆኑን በመጥቀስ በሌሎች የተፋሰሱ አገራት የሚነሱ ጉዳዮች በውይይትና ድርድር ዕልባት እንደሚያገኝ እምነታቸው መሆኑን አመልክተዋል።
ሁለቱ አምባሳደሮች በደቡብ አፍሪካ ቆይታቸው በጥሩ መሠረት ላይ የተገነባውን የሁለቱን አገራት ግንኙነት ይበልጥ በማጎልበት የህዝቦችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በጋራ እንደሚሠሩ አረጋግጠዋል።