በክቡር አምባሳደር ዶ/ር ሙክታር ከድር የተመራ የልዑካን ቡድን በኢስተርንኬፕ-ፕሮቪንስ፤ ፖርትኤሳቤትና አካባቢው ከሚገኙ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አባላት ጋር በዜጎች መብትና ደህንነት ማስጠበቅ፣ በዳያስፖራ ልማትና ተሳትፎ እንዲሁም በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮችን ዙሪያ ውይይት አካሂዷል።
በውይይቱ ኤምባሲው በሀገሪቱ የሚገኙ ዜጎች መብትና ጥቅም ማስጠበቅ፣ በዳያስፖራ ልማትና ተሳትፎ እንዲሁም በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ እያደረገ ያሉትን ሥራዎች ገለጻ የቀረበ ሲሆን ዝርዝር ውይይት ተደርጎበታል፡፡
በአካባቢው የሚገኙ ዜጎች ጠንካራ አደረጃጀት በማቋቋም እያጋጠሟቸው ያሉት የጋራ ችግሮችን ለመቅረፍ ከኤምባሲው እና ከአካባቢው ማህበረሰብና የሀገሪቱ የአስተዳደር አካላት ጋር በቅርበት በመቀናጀት እየተንቀሳቀሱ መሆኑ በተሳታፊዎች በስፋት ተገልጿል፡፡ ጥረቱም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ተጠቁሟል፡፡
በወቅቱም በተለይም በዜጎችቻችን የሥራና ደህንነት ሥጋቶችን የሚደቅኑ እና ሀገራዊ ገጽታን በሚያጠለሽ ድርጊቶች ውስጥ አንዳንድ የዳያስፖራ አባላት መኖራቸው በተሳታፊዎች የተገለጸ ሲሆን፤ ከድርጊቶቻቸው እንዲቆጠቡ መልዕክት ተላልፏል፡፡ ከዚሁ ጋር በተገናኘ በሁለቱ ሀገራት መካከል በወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦችን አሳልፎ ለመስጠት የሚያስያችል ስምምነት በቅርቡ የተፈረመ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡
እንዲሁም በአሁኑ ወቅት በአንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢዎች በተደራጁ ህገወጥ ቡድኖች አማካኝነት በዜጎቻችን የንግድ መደብሮች ላይ የሚፈጸሙ ህገወጥ ድርጊቶችን ለመከላከል ከየአካበቢው ማህበረሰብና የአስተዳደር መዋቅር ጋር የተጀመረውን መስተጋብርና የትብብር እንቅስቃሴ አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ ተጠቁሟል፡፡
በተጨማሪም መንግስት በውጭ ለሚኖሩ የዳያስፖራ አባላት በሀገር ቤት በተለያዩ የልማት ዘርፎች እንዲሳተፉ በፖሊሲ የተደገፈ አሰራሮችን ዘርግቶ እያበረታታና እያስፈጸመ እንደሚገኝ የተገለጸ ሲሆን፣ ዳያስፖራው ዕድሎቹን በመጠቀምና ተሳትፎአቸውን በማጠናከር ራሳቸውንና ሀገራቸውን ተጠቃሚ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀርቧል፡፡
በአጠቃላይ በፖርትኤልሳቤትና አካባቢው የሚገኙ ዜጎቻችን አደረጃጀቶቻቸውን በማጠናከር ከኤምባሲውና ከአካባቢው የአስተዳደር አካላት ጋር ያሏቸውን ጠንካራና የትብብር እንቅስቃሴዎች አጠናክሮ ለማስቀጠል መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡