እኛ ኢትዮጵያዊያን የባለብዙ ባህል፣ ታሪክ፣ ሀይማኖት፣ መልከዐ-ምድራዊ አቀማመጥና የአስተሳሰብ ብዛሃነት ያለን ነን፡፡ ይህ ግን ለዘመናት የቆየውን ህብረታችነና አንድነታችንን አላጠፋውም፡፡ ብዛሃነታችን በአግባቡ ሲያዝና እውቅና ሲሰጠው፤ እንዲሁም ደግሞ ሀገራዊ አንድነትና ኅብረት እንዲያብብና እንዲጎለብት ስንተጋና በትልቅነትና በጋራ ማንነት ውስጥ ያለውን ሃያልነት ከአድዋ፣ ከህዳሴ ግድባችን እና ከሌሎች የጋራ ፕሮጀክቶቻችን መማር ከቻልን እንደ አገር ያሰብነውን ለማሳካት የሚያስችለን አቅምና ኃይል እንዳለን እንረዳለን፡፡ ሌሎችም እንዲረዱን እናደርጋለን፡፡ በጋራ ስንቆም የድርድርና የማሸነፍ ግርማ ሞጎሳችን በዚህ ልክ ደምቆ ይታያል።
 
ከዚህና ከሌሎች መሠረታዊ እሳቤዎች በመነሳት ከጋራ ችግራችን በላይ የጋራ አቅማችን እንደሚያይል በመረዳት ከፉክክር ወጥተን ትብብርን መርህ ማድረግ፣ አልፈንም ሰላማዊና ፖለቲካዊ አማራጮችን ያስቀደመ የመፍተሔ ሐሳብ በሀገራችን እንዲያሸንፉ ማድረግ ብቸኛና ትክክለኛ ጎዳና ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያን ራሳቸው ባለቤት የሆኑበት፣ አፍሪካ-መሪ ድርድር በደቡብ አፍሪካ አስተናጋጅነት (Host) ተካሂዷል፡፡ በዚህም ታሪካዊ የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ተፈርሟል፡፡ የፌዴራል መንግስት በዚህ ጉዳይ ላይ የፊታውራርነት ድርሻ የተወጣበት ሲሆን፣ የዛሬ ዓመት በያዝነው ሳምንት ይህ ታሪካዊ ተግባር ተከናውኗል፡፡ ስምምነቱ ችግሮችን በሰላም የመፍታት፣ ለፖለቲካዊ መፍተሄዎች ቅድሚያ መስጠት፣ ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍተሄ መስጠትን፣ ለችግሮች ዘላቂና ሰላማዊ መፍተሄ መፈለግን፣ ወዘተ.. ጉዳዮችን በዋናነት የያዘ ነበረ።
 
ስምምነቱ እኛ ኢትዮጵያዊን ችግሮቻችን በራሳችን የመፍታት አቅምና ቀናነት እንዳለን ያሳየን ሲሆን፣ እስካሁን በቃል (rhetoric) ብቻ የሚተወቀውን “የአፍሪካን ችግር በአፍሪካዊያንና በአፍሪካዊ መንገድ መፍታት” የሚለውን መሠረታዊ መርሆ ከቃል ያለፈ ፋይዳ የለውም ሲባል የነበረውን እሳቤ በመሻር፣ አፍሪካዊ ዕሳቤው ህይወት እንዲዘራ በማድረጋችን እንደተለመደው ለጋራ ውሳኔም ጭምር ፈርቀዳጅ ሚና መጫወት ተችሏል፡፡ በጥቅሉ ግን በዚህ ስምምነት ምክንያት በሰሜኑ የአገራችን ክፍል ሰላማዊና ፖለቲካዊ ሂደቶች ስፍራ መያዝ ችለዋል፡፡ ይህም ታላቅ የጋራ ስኬታችን ነው።
 
ኢትዮጵያ ውስጥ የኃይል አማራጭ ስፍራ የለውም፡፡ ማንኛውንም ዓይነት ጥያቄና ቅሬታ በሰላማዊ መንገድ መፍታት ሱልጡንነት ነው፣ በመሆኑም የፕሪቶሪያ ሰላም ስምምነት እየነገረን ያለው ይሄን ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ጋር በማያያዝ የኤምባሲው ጠቅላላ ሰራተኞ፣ ዲፕሎማቶችና የስራ ኃላፊዎች የሰላም ስምምነቱን አንድ አመት ምክንያት በማድረግ የፓናል ውይይት አድርገዋል፡፡ በዚህም የሰላም ስምምነቱ ለሀገራዊ አንድነታችን፣ ለኢኮኖሚያዊ እድገታችን፣ ለማህበራዊ ትስስራችን፣ እንዲሁም ለሁለትዮሽና ለባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲያችን ሥራችን ላይ ትልቅ እገዛ እንዳለው ተወስቷል።
ሰላምና ብልጽግና ለኢትዮጵያችን!
 
ጥቅምት 22 ቀን 2016 ዓ/ም
(02 November 2023) ደቡብ አፍሪካ፣ ፕሪቶሪያ

Disclaimer: The official text of the Embassy Website is the English language version. Any discrepancies or differences created in translations are not binding and have no legal effect for compliance or enforcement purposes.

X
Twitter
Facebook
YouTube
Instagram