ክቡር አምባሳደር ዶ/ር ሙክታር ከድር KUSALA GREEN BIODIVERSITY ORGANIZATION የተባለው ድርጅት መስራች፣ የዳይሬክተሮች ቦርድ አመራር አባል እና Climate Change Specialist የሆኑት Mrs. Sentle Tabane በአገራችን ወቅታዊ ጉዳዮች፣በአገራችን የቱሪስት መስህብ ቦታዎች ፖቴንሽያልና አጠባበቅ፣በአየር ንብረት ለውጥና በአፍሪካዊ የጋራ ጉዳዮቻችን ላይ በጣም ጠቃሚ የሚባል ውይይት አካሂደዋል፡፡
ክቡር አምባሳደር በዚሁ ወቅት የአገራችን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ በዝርዝር ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡በህወሃት የተፈጠረው ጦርነት እንዳይጀመር አገራችን ያለፈችባቸውን በትዕግስት የተሞሉ ጊዜያት፣ተገደን የገባንበት ጦርነት እንደሆነና አሁን ጦርነቱ ቆሞ በአፍሪካ ህብረት ጥላ ሰር የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ኦሊሴጎን ኦባሳንጆ አደራዳሪነት ጉዳዩ እልባት ሊያገኝ በሂደት ላይ መሆኑን፣ በዚሁም መሰረት በኢትዮጵያ በኩል በክቡር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር የሚመራ 7 አባላት ያሉት የሰላም ተደራዳሪ ኮሚቴ ተደራጅቶ እየሰራ እንደሆነ፣ኢትዮጵያ ጦርነት የማትፈልግና ሁሌም ለሰላም ቁርጠኝነት እንዳላት አስረድተዋል፡፡እውነታው ይህ ቢሆንም በተሳሳተ ትርክት ላይ በመመስረት ታዋቂ ነን የሚሉ ሚዲያዎች አንዳንድ ምዕራባውያን አገሮችን እያሳሳቱት መሆኑን በማስረዳት ስለኢትዮጵያ በተገቢው ሁኔታ ትክክለኛውን መረጃ ሰጥተዋል፡፡
ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ዝቅተኛ አሉታዊ አስተዋጽዖ ያላት ሆና ሳለ በከፍተኛ ደረጃ ተጎጅ መሆኗን፣በዚህም ምክንያት ድርቅ እና የተለያዩ ጉዳቶች ሰለባ እንደሆነች፣ይህንኑ ታሳቢ በማድርግ አገራችን Green Development Strategy አውጥታ እየተገበረች እንደሆነ፤ኢትዮጵያ በአፍሪካ ፈጣን እድገት ከሚያስመዘግቡ ጥቂት አገራት አንዷ መሆኗን፣ የእድገቱን ቀጣይነት ለማረጋገጥ፣የግብርና መር ኢንደስተሪያላይዜሽን ጉዟችን ለማቀላጠፍ የኃይል አቅርቦት ማሳደግ ቁልፍ ተፈላጊነት ያለው ጉዳይ እንደሆነ፣ አገራችን ከፍተኛ የሆነ የታዳሽ ኃይል ፖቴንሽያል ያላት አገር እንደመሆኗ መጠን ይህንኑ የውሃ፣የንፋስና የጅኦ ተርማል ዕምቅ አቅም በመጠቀም ሃይል የማመንጨት ስራ እየሰራች መሆኑን፣በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ መሪነት ኢትዮጵያን አረንጓዴ የማልበስ/GREEN LEGACY/ መርሃ-ግብር ተነድፎ ባለፉት 3 ዓመታት 20 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን በተሳተፉበት ከ18 ቢሊዮን በላይ ዛፎች የተተከሉ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ ችግሩ የጋራ እንደመሆኑ መጠን መፍትሔውም የጋራ ነው በሚል አስተሳሰብ በመመራት ይህንኑ አረንጓዴ የማልበስ መልካም ተግባር በጎረቤት አገሮች በደቡብ ሱዳን፣በሶማሊያና በጅቡቲ የኢትዮጵያን ልምድ ለማስፋፋት የምስራቅ አፍሪካን የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳት የመታደግ የተቀናጁ ጥረቶች እየተካሄዱ ናቸው፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ/ GERD/ የታዳሽ ኃይል ማመንጫ ከሆኑት አንዱ ፕሮጄክት መሆኑን፣ፕሮጄክቱ ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያውያን ባለቤትነትና ፋይናንስ እየተካሄደ መሆኑን፣ኢትዮጵያ የውሃው 86 በመቶ አመንጭ እንደሆነች፣ፕሮጄክቱን የምትገነባው ከህዝቧ ከ70 በመቶ በላይ ያለመብራት የሚኖረውን ህዝቧን የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ለማድረግና በድህነት ውስጥ የሚገኘውን 60 በመቶ ህዝቧን ከድህነት ለማላቀቅ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ግብጽና ሱዳን የግድቡን ጉዳይ ወደ ተባበሩት መንግስታት መድረኮች ለመወሰድ ተደጋጋሚ ጥረት ኢትዮጵያ በጽኑ በምታምንበት ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ መርህ በመመራት ድርድሩ በአህጉራዊ ድርጅታችን የአፍሪካ ህብረት ማዕቀፍ ስር እንዲካሄድ በማድረግ አፍሪካውያን የራሳቸውን ችግር በራሳቸው ለመፍታት የሚያስችል ብቃት እንዳላቸው የሚያጸና አቅጣጫ ተከትላለች፡፡
Mrs. Sentle Tabane በበኩላቸው ለተደረገላቸው ዝርዝር ማብራሪያ ከልብ አመስግነው፣ እርሳቸው ተፈጥሮን የሚያደንቁ በመሆናቸው ከአካባቢ ጥበቃ ላይ የሚሰራ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት አቋቁመው እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ሄደው የቱሪስት መስህቦችን መጎብኘታቸውን፣ኢትዮጵያውያን ሃገራቸውን የሚወዱ፣ በስራ ታታሪና ኩሩ ህዝቦች መሆናቸውን እንደተገነዘቡ ገልጸው በኢትዮጵያ ሰላም ሰፍኖ ማየት ምኞታቸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡ከዚሁም በተጨማሪ አፍሪካ በርካታ ጸጋዎች ያሏት ቢሆንም ወደ ፊት እንዳትራመድ የሚያደርጓት የውጭ ኃይሎች እንዳሉ፣ኢትዮጵያ ለቱሪዝም የተመቸች አገር መሆኗን፣በኢትዮጵያ በስፋት የበቀለውን ባህርዛፍ ጎጅ ተጽእኖ ለማቃለል ከደቡብ አፍሪካ መልካም ተሞክሮ ለማካፈል ዝግጁ መሆናቸውን፣ ኢትዮጵያን የተመለከቱ ወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ብዙ ተመልካች ያላቸው እንደነ ቢቢሲ ያሉ የሚዲያ ተቋማት ትክክለኛውን ሳይሆን ሃሰተኛውን መረጃ እንደሚጠያሰራጩ፣በሌላ በኩል ኢትዮጵያውያን እውነታውንና ጸጋወቻቸውን በሚፈለገው ደረጃ ማስተዋወቅ ረገድ ብዙ መስራት ይጠበቅባቸዋል፣ ኢትዮጵያ የፓሪስ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ ፈራሚ እንደመሆኗ መጠን Mitigation & Adaptation Programs ተጠቃሚ መሆን እንደምትችል በዚሁም ረገድ KUSALA GREEN BIODIVERSITY ORGANIZATION ከኢትዮጵያ ጋር ተቀራርቦ ለመስራት ፍላጎት እንዳለው ገልጸዋል፡፡ በዚሁም ወቅት ኢትዮጵያ በአካባቢ ጥበቃ ረገድ እያደረገች ያለችውን ጥረት አድንቀዋል፡፡ ከዚሁም በተጨማሪ የሚኖሩበትን የኖርዝ ዌስት ፕሮቪንስ ክቡር አምባሳደራችን እንዲጎበኙ ጋብዘዋቸዋል፡፡
ክቡር አምባሳደርም የቀረበላቸው አስተያየት ጠቃሚና ተቀባይነት ያለው መሆኑን በመግለጽ ሚሲዮናችን ከድርጅታቸው ጋር ተቀራርቦ ለመስራት ያለውን ዝግጁነትና ቁርጠኛነት አረጋግጠውላቸዋል፡፡ ለቅንጅት ለተሞክሮ ልውውጥና ተያያዥ ጠቀሜታዎች ሲባል ኢትዮጵያ የሚገኘው የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን/Ethiopian Environmental Protection Authority/፣ KUSALA GREEN BIODIVERSITY ORGANIZATION እና ሚሲዮኑ የሚሳተፉበት ቨርቹዋል መድረክ እንደሚያዘጋጁ ተናግረዋል፡፡ ለተደረገላቸው ግብዣም አመስግነው ተገቢ ፕሮግራም ተይዞ እንደሚፈጸም ቃል ገብተዋል፡፡

Disclaimer: The official text of the Embassy Website is the English language version. Any discrepancies or differences created in translations are not binding and have no legal effect for compliance or enforcement purposes.

X
Twitter
Facebook
YouTube
Instagram