በክቡር የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ነሐሴ 18 ቀን 2015 ዓ.ም በይፋ የተመረቀው በፕሪቶሪያ የኢትዮጵያ አምባሳደር መኖሪያ የማስተዋወቅና የምስጋና ፕሮግራም ተካሄደ።
ፕሮግራሙ ክብርት አምባሳደር ብርቱካን አያኖ፣ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ፣ ክብርት Ms Mashego-Dlamini፣ የደቡብ አፍሪካ ዓለምአቀፍ ግንኙነትና ትብብር ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስትር እና የሚኒስቴሩ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ ክቡር አምባሳደር ዶ/ር ሙክታር ከድር፤ በደቡብ አፍሪካ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር፣ ተቀማጭነታቸው በደቡብ አፍሪካ የሆኑ የአፍሪካ አገራት አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች፣ በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበራት ተወካዮች፣ የሃይማኖት አባቶች/መሪዎች፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሰራተኞች፣ የሚዲያ አካላት እና የኤምባሲው ሰራተኞች በተገኙበት በደማቅ ሁኔታ ተከናውኗል።
 
በወቅቱም ክብርት አምባሳደር ብርቱካን የፕሮግራሙ ታዳሚዎችን ያመሰገኑ ሲሆን፤ የኢትዮጵያና ደቡብ አፍሪካ ግንኙነት ታሪካዊና በሁሉም የግንኙነት አግባቦች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጎለበተ መምጣቱን፣ በቅርቡ የተደረገውን የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት፣ በባለፈው ጁላይ ወር 2023 መጨረሻ በአዲስ አበባ የተደረገው 4ኛው የኢትዮጵያና ደቡብ አፍሪካ የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽን ስብሳባ በስኬት መካሄዱን፣ ሁለቱ አገራት በአህጉራዊና በዓለምአቀፋዊ የጋራ ጉዳዪች ዙሪያም በቅርበትና በትብብር እየተንቀሳቀሱ የሚገኙ መሆኑን፣ እንዲሁም በደቡብ አፍሪካ አስተናጋጅነት በተካሄደው 15ኛው የብሪክስ የመሪዎች ጉባኤ ወቅት አገራችን ጥምረቱን በይፋ የተቀላቀለችበትን መልካም አጋጣሚ ለአብነት በመጥቀስ ግንኙነቱ ወደ ስትራቴጂካዊ አጋርነት ደረጃ ያደገ መሆኑን በመግለጽ፤ ህንጻው ለቀጣይ የተጠናከረ የግንኙነት እንቅስቃሴ መደላድል የሚፈጥር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
 
ክብርት Ms Mashego-Dlamini በበኩላቸው የህንጻም መጠናቀቅና መመረቅ እንዳስደሰታቸውና የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕት አቅርበዋል፡፡ እንዲሁም የሁለቱ አገራት ግንኙት ታሪካዊ መሆኑን፣ በተለይም ኢትዮጵያ ለደቡብ አፍሪካ የነጻነት ትግል ወቅት ትግሉን ሲመሩ ለነበሩ ለኔልሰን ማንዴላና ለትግል አጋራቸው አስፈላጊውን ሁሉ የወታደራዊ ስልጠና እና የሞራል ድጋፍ ማድረጓን ለዚህም የደቡብ አፍሪካ መንግስትና ህዝብ ሁሉ ጊዜም ልዩ ስፍራ የሚሰጠው መሆኑን፣ የሁለትዮሽ ግንኙነቱ በሁሉም ዘርፎች እየተጠናከረ መምጣቱንና በጋራ የበይነመንግስታት አጀንዳዎች ላይም ጭምር በትብብር እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙ፣ አገራቸው ደቡብ አፍሪካ የአገራችን የሰሜኑ ግጭት በሰላም እንዲቋጭ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍና ትብብር ያደረገች መሆኗን በመጥቀስ፤ በተመሳሳይ በጎረቤት አገር በሱዳን የተቀሰቀሰው ግጭት በሰላም እንዲቋጭ ጥረት እያደረጉ መሆኑን አንስተዋል፡፡ የሁለትዪሽ ግንኙነቱም ይበልጥ እንዲጠናከር ሚኒስቴር መስሪያ ቤታቸው ከኤምባሲው ጋር በቅርበትና በትብብር እየሰሩ እንደሚገኙም አክለው ገልጸዋል።
 
ክቡር አምባሳደር ዶ/ር ሙክታር በበኩላቸው በፕሮግራሙ ለተገኙት ክቡራን ሚኒስትሮች፣ አምባሳደሮችና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች እንኳን ደህና መጣችሁ በማለት የሁለቱ አገራት ግንኙነት ታሪካዊ ዳራ በማንሳት ግንኙነቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጎለበተ መምጣቱንና በተለይም በአሁኑ ወቅት ወደ ስትራቴጂካዊ አጋርነት ደረጃ መድረሱን ጠቁመዋል፡፡ መኖሪያ ህንጻው ይህንኑ የሚያንጸባርቅና ለቀጣይ የተጠናከ ሥራ ምቹ ሁኔታዎችን የሚፈጠር መሆኑንም አክለው ገልጸዋል፡፡
 
በመጨረሻም ህንጻውን በታቀደው ጊዜና የጥራት ደረጃ ተገንብቶ እንዲጠናቀቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱት አካላት የላቀ ምስጋና የቀረበ ሲሆን ፕሮግራሙን ምክንያት በማድረግ በተዘጋጀው የእራት ግብዣ ፕሮግራሙ ተጠናቋል፡፡

Disclaimer: The official text of the Embassy Website is the English language version. Any discrepancies or differences created in translations are not binding and have no legal effect for compliance or enforcement purposes.

X
Twitter
Facebook
YouTube
Instagram