በደቡብ አፍሪካ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ዶ/ር ሙክታር ከድር የተመራ ልዑክ በኢስዋቲኒ ከሚኖሩ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አባላት ጋር ተወያየ፡፡
በውይይቱ ሚሲዮኑ ለዜጎች በሚሰጣቸው የኢሚግሬሽንና የቆንስላ አገልግሎቶች፣ የዳያስፖራ ልማትና ተሳትፎ ሥራዎች እንዲሁም በሌሎች የጋራ ጉዳዮች ዙሪያ ጠቃሚ ምክክር በማድረግና ግንዘቤ በመፍጠር በቀጣይ የተጠናከረ የትብብር እንቅስቃሴዎችን ለማድረግ የጋራ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡
በወቅቱም አምባሳደር ዶ/ር ሙክታር በኢስዋቲኒ የኢትየጵያዊያን ኮሚኒቲ ማህበር ጥሩ እንቅስቃሴ እያደረገ እንደሚገኝ በመጠቆም፤ ማህበሩን ይበልጥ ማጠናከር የዳያስፖራውን የጋራ ማህበራዊ ጉዳዮችን ለመከወንና ከአገሩ ጋር ያለውን ሁለንተናዊ ትስስር ለማጎልበት እንዲሁም በሚኖሩበት አገር የዜጎችንና የአገራችንን መልካም ገጽታ ለማስተዋወቅና ለመገንባት የላቀ አስተዋጽኦ የሚያበረክት መሆኑን በአጽንኦት አስገንዝበዋል፡፡
የማህበሩ አመራሮችና የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ልዑኩ በኢስዋቲኒ በመገኘት ላመቻቸው የገጽ ለገጽ የጋራ የምክክር መድረክ በማመስገን፤ ማህበሩን በማጠናከር በአገራዊ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ተሳትፎ ለማጎልበት ዝግጁነታቸውን አረጋግጠዋል፡፡
እንዲሁም ሚሲዮኑና በአገር ቤት የሚገኙ የመንግስት ተቋማት ለተገልጋዮች ከሚሰጧቸው የተለያዩ አገልግሎቶች አሰጣጥ ጋር በተገናኘ እያጋጠማቸው ያሉትን ችግሮች በመጠቆም እንዲቀረፉ ጠይቀዋል፡፡
ሚሲዮኑ ለቀረቡት ጥቆማዎች ልዩ ትኩረት በመስጠት ችግሮቹ ለመቅረፍ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅርብት እየሰራ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡
ኢስዋቲኒ ሚሲዮኑ ከሚሸፍናቸው የደቡባዊ አፍሪካ አገራት አንዷ ስትሆን፣ በአገሪቱ በተለያዩ ተቋማት በማገልገል ላይ የሚገኙ ከፍተኛ ባለሙያዎች እንዲሁም በቢዝነስ ሥራዎች የተሰማሩ የዳያስፖራ አባላት ይገኛሉ፡፡