የዘንድሮውን ዓለምቀአቀፍ የሴቶች ቀን (March-8/2023) “እኔ የእህቴ ጠባቂ ነኝ” በሚል መሪ ቃል ክቡር አምባሳደር ዶ/ር ሙክታር ከድር፣ በደቡብ አፍሪካ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር፣ የኤምባሲው ሰራተኞች እንዲሁም በርካታ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በተሳተፉበት በደማቅ ሁኔታ ተከበረ፡፡
የዓለምቀአቀፍ የሴቶች ቀን በዓለም ላይ ለሚገኙ ሴቶች የእኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት መከበር መሰረት የጣለ መሆኑን፣ በአገራችንም የሴቶችን እኩልነት፣ ፍትሃዊ ተጠቃሚነትና ሁለንተናዊ ተሳትፎ ሊያረጋግጡ የሚያስችሉ ተጨባጭ እርምጃዎች መወሰዳቸውና ውጤታማነታቸው በተግባር እየተረጋገጠ መምጣቱን ክቡር አምባሳደር ዶ/ር ሙክታር በዓሉን በማስመልከት ባስተላለፉት መልዕክት ገልጸዋል፡፡
በደቡብ አፍሪካም በርካታ ሴት ኢትዮጵያዊያን ዳያስፖራ አባላት የሚገኙ መሆናቸውና የጋራ ማህበራዊ ጉዳዮቻቸውን በህብረት ለመከወን እንዲችሉ ያደራጁት የሴቶች ማህበር አጠናክረው መንቀሳቀስ እንደሚገባቸው፣ ለዚህም ኤምባሲው እያደረገ ያለውን አስፈላጊ ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ክቡር አምባሳደር አረጋግጠዋል፡፡
የMarch-8 በዓል መነሻ ምክንያቶችና ለመላው ሴቶች ያጎናጸፋቸውን ትሩፋቶች እንዲሁም በዚሁም መነሻ በተለይም በአገራችንና በደቡብ አፍሪካ ለሚገኙ ሴት የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አባላት ያሏቸውን የጋራ ጉዳዮች በህብረት ለመተግበር እንዲችሉ ጠንካራ አደረጃጀት ፈጥሮ መንቀሳቀስ ወቅቱ የሚጠይቀው ወሳኝ ጉዳይ ሊሆን እንደሚገባ የሚጠቁሙ ገለጻና ተሞክሮዎች በበዓሉ ተሳታፊ የዳያስፖራ አባላት ቀርቧል፡፡
በዓሉ በኤምባሲ አዘጋጅነትና በሴት የዳያስፖራ አባላት ተባባሪነት በስኬት የተከናወነ ሲሆን ለዚህም ኤምባሲው የላቀ ምስጋና ለማቅረብ ይወዳል፡፡