በደቡብ አፍሪካ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ልዩ መልእክተኛና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ክቡር ዶ/ር ሙክታር ከድር የካዋዙሉ ናታን ፕሮቪንስ ዋና ከተማ ፒተርማርዝበርግ ከንቲባ Councilor Mzimkhulu Thebolla፣ ምክትል ከንቲባ Councilor Mxolisi Mkhize፣ አፈጉባኤ Eunice Majola እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችን በማግኘት በህዝብ ለህዝብ፣ በሁለትዮሽ ትብብሮች እንዲሁም በአገራችን ወቅታዊ ጉዳች ዙሪያ ጠቃሚ ውይይት አድርገዋል፡፡
ክቡር አምባሳደሩ በውይይቱ የኢትዮጵያ እና የደቡብ አፍሪካ ግንኙነትን ታሪካዊና ለመላው ጥቁር ህዝቦች የነጻነት ተጋድሎ ፋና ወጊ ከሆነው የአድዋ ድል ጀምሮ መሆኑንና ኢትዮጵያ ኔልሰን ማንዴላን ጨምሮ ለሌሎችም የአፍሪካ አገራት ከጭቆና ቀንበር ለመላቀቅ ትግሉን ሲመሩት ለነበሩት የነጻነት ታጋይ አባቶች የሰጠችው ወታደራዊ ስልጠናዎችና የተለያዩ ድጋፎችን በመጥቀስ የሁለቱ አገራት ግንኙነት ታሪካዊና በአፍሪካዊ ወንድማማችነት መሰረት ላይ የተመሰረተ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የፒተርማርዝበርግ ከተማ ጨምሮ በደቡብ አፍሪካ ሰፊ ቁጥር ያለው ኢትዮጵያዊያን እንደሚገኙና የአገሪቱ መንግስትና ህዝብ ዜጎቻችንን ተቀብሎ በማስተናገዳቸው የላቀ ምስጋና አቅርበዋል፡፡ ይህም አፍሪካዊ ወንድማማችነት ተምሳሌታዊ ግንኙነት ይበልጥ እንዲጠናከር ከከተማ መስተዳደሩ ጋር በትብብር ለመስራት ዕቅድ እንዳላቸውም አምባሳደሩ ገልጸዋል፡፡
በአገራችን ወቅታዊ ሁኔታ አስምልክቶ አምባሳደሩ ለባለሥልጣናቱ ዝርዝር ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ክቡር ከንቲባ Councilor Mzimkhulu Thebolla በበኩላቸው ክቡር አምባሳደር በከተማዋ በመገኘት በሁለቱ አገራት ታሪካዊ ግንኙነት፣ የህዝብ ለህዝብ ትስስር፣ በሁለትዮሽ ትብብሮች ዙሪያ በቅርበት ለመስራት ላሳዩት ፍላጎት ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
Councilor Mzimkhulu በወቅቱ ኢትዮጵያ ለመላው አፍሪካ የነጻነት ንቅናቄን ጨምሮ በደቡብ አፍሪካ ጸረ አፓርታይድ ትግል ወቅት ለነጻነት ታጋዮች ድጋፎን በመስጠት ጭምር ለተጫወተችው ታሪካዊ ሚና በደቡብ አፍሪካ መንግስትና ህዝብ ዘንድ ትልቅ ሥፍራ የሚሰጠው መሆኑን በማውሳት የላቀ ምስጋና አቅርብዋል፡፡
ኢትዮጵያ በብዙ መልኩ ለየት ያሉ ታሪኮች ያሏት አገር መሆኗን፣ ለቅኝ ገዥ ፋሺስቶች ያለተንበረከከችና ያልተገዛች ለመላው ጥቁር ህዝቦች የነጻነት ቀንዲል መሆኗን ጠንቅቀው እንደሚያውቁ የጠቀሱት ምክትል ከንቲባ Councilor Mxolisi Mkhize፣ ኢትዮጵያ በወቅቱ ለጸረ ቅኝ ግዛት ትግሎች ያደረገችው ተጨባጭ የሞራል፣ የስልጠና እና ሌሎች የተለያዩ ድጋፎች ለዛሬዋ ደቡብ አፍሪካ ነጻ አገር መወለድ ጉልዕ ሚና እንደነበረውና ይህም ታሪካዊ ሃቅ በደቡብ አፍሪካ ህዝብ ሁሉጊዜም ልዩ ትርጉምና ሥፍራ የሚሰጠው እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ይህችን ታሪካዊ የአፍሪካ መናገሻ ኢትዮጵያን በአካል ለመጎብኘት ጽኑ ፍላጎትና ዕቅድ እንዳላቸውም አክለው ገልጸዋል፡፡
በከተማዋ ሰፊ ቁጥር ያላቸው ኢትዮጵያዊን በቢዝነስ ሥራ ላይ ተሰማርተው የሚገኙ መሆናቸው፣ በሥራ ታታሪነታቸው፣ በመልካም ስነምግባራቸውና ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር ባላቸው ቅርርብ የሚወደሱና የሚመሰገኑ መሆናቸውን የጠቀሱት Councilor Mzimkhulu በተለያዩ የጋራ ጉዳዮች ዙሪያ ከኢትዮጵያዊያኑ ጋር በማናቸውም ሰዓት በራቸውን ክፍት በማድረግ እየተስተናገዱ እንደሚገኙና ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም የከተማ መስተዳድሩ የመንግስት ለመንግስት፣ የከተሞች፣ የቢዝነስ እና የሌሎችም ዘርፎች በትብብር ለመስራት የሚያስችሉ ጉድኝቶችን ፈጥሮ ለመንቀሳቀስ ልዩ ትኩረት እንደሚሰጥና ለዚህም ከኤምባሲው ጋር ተቀራርቦ ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን ከንቲባው አክለው ገልጸዋል፡፡
ከወቅታዊ ጉዳዮች ጋር ተያይዞ የቀረበላቸው ዝርዝር ማብራሪያ ግልጽና ግንዘቤ የፈጠረላቸው መሆኑን ጠቁመው፣ ኢትዮጵያ የገጠማትን ወቅታዊ ችግር በመፍታት የልማት ጉዞዋን እንደምታፋጥን ያላቸውን እምነት ባለሥልጣናቱ ገልጸዋል፡፡