እ.ኤ.አ ከ Feb 6-8 በፕሪቶሪያ ዩኒቨርሲቲ በሚካሄደው United States-Africa University Partnership Initiative Summit የተባበሩት መንግስታትን የዘላቂ ልማት ግቦች ላይ የተመሰረተ Equitable and Sustainable Partnerships for Impact በሚል መርህ ቃል ለሚደረገው ጉባኤ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ የትምሀርት ሚኒስቴር የአስተዳደርና መሰረተ ልማት ዋና ስራ አስኪያጅ የሆኑት ዶ/ር ሰለሞን አብርሀ የተመራ የልዑካን ቡድን እየተሳተፈ ይገኛል። በፕሪቶሪያ ዩኒቨርሲቲ አስተናጋጅነት በሚካሄደው በዚሁ ጉባኤ ላይ እየተሳተፈ ያለው ልኡክ የደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ታፈረ መላኩ፣ የባሀርዳር ዩኒቨርሲቲ የምርምር እና ማህበራዊ አገልግሎቶች ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ተስፋዬ ሽፈራው ፣ በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር አብዲ አህመድን በአባልነት አካቶዋል።
በደቡብ አፍሪካ የኢፌዲሪ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ዶ/ር ሙክታር ከድር ከልዑካን ቡድኑ ጋር የሀገራችን ዩኒቨርሲቲዎች ከደቡበ አፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎችና ተቋማት ጋር የሚያደርጉትን የጉድኝት ስራዎች በተመለከተ ተቋማቱ እንዲሁም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከኤምባሲው ጋር ተቀራርበው መስራት በሚችሉባቸው ጉዳዩች ዙሪያ ውይይት አድርገዋል። የልኡካን ቡድኑ ከደቡብ አፍሪካ የትምህርት ተቋማት ጋር በቅርበት ለመስራት የሚመሩት ተቋማት ፍላጎት እንደሆነ በመግለፅ ከሚስዮኑ ጋር በጋራ ለመስራት ከስምምነት ተደርሷል።ክቡር አምባሳደሩ በበኩላቸው ደቡብ አፍሪካና ኢትዮጵያ ያላቸውን ወዳጅነት እንደ ምቹ ሁኔታ በመጠቀም በከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ ትብብሩን በማሳደግ ሁለቱም አገሮች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ አብራርተው በደቡብ አፍሪካ የኢፌዴሪ ኤምባሲ ለግንኙነቱ መጎልበት የሚያስፈልገውን ተልዕኮ ለማሳካት ዝግጁ መሆኑን በማረጋገጥ በጉዳዩ ላይ ተገቢውን ትኩረት ሰጥተው አንደሚሰሩ ገልፀዋል።