ኤምባሲው በናሚቢያ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ማኀበር አባላት ጋር ተወያየ፤
የማኀበሩ አባላት በአገራዊ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ሁለንተናዊ ተሳትፎ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል፤
በሚሲዮኑ ምክትል መሪ አቶ ሙሉጌታ ውለታው የተመራ፣ የዳያስፖራ ተሳትፎና ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ እንዲሁም የፖለቲካና የአገር ገጽታ ግንባታ ዘርፎች የሥራ ኃላፊዎችን ያካተተ የልዑካን ቡድን ወደ ናሚቢያ- ዊንድሆክ እ.ኤ.አ ከጁላይ 20 እስከ 23 ቀን 2022 ተንቀሳቅሶ የኢትዮጵያና ናሚቢያ የሁለትዮሽ ግንኙነት የሚያጠናክሩ እና በአገሪቱ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አባላትን በሚመለከቱ ጉዳዮች ዙሪያ ውጤታማ ሥራዎች አከናውኗል፡፡
ልዑኩ በቆይታው በናሚቢያ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ማኀበር (Ethiopian Community Association in Namibia-ECAN) አባላት ጋር እ.ኤ.አ ጁላይ 22 ቀን 2022 በመገናኘት በማህበሩ አጠቃላይ የሥራ እንቅስቃሴ፣ በአገራችን ወቅታዊ ጉዳዮች፣ ለወቅታዊ አገራዊ ጥሪዎች አባላቱ እያደረጉት ያለው ተሳትፎ፣ ኤምባሲው ለዜጎች በሚሰጣቸው የተለያዩ አገልግሎቶች እንዲሁም በሌሎችም የጋራ ጉዳዮች ዙሪያ ጠቃሚና ግልጽ ምክክር አካሂዷል፡፡
በምክክሩ መግቢያ ላይ በናሚቢያ የክብር ቆንስል የሆኑት ዶ/ር ማርታ ጥላሁን የእንኩዋን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን በናሚቢያ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ማኀበር በአገሪቱ ህግና አሰራር መሰረት ተመዝግቦና ህጋዊ ሰውነት አገንኝቶ በተለያዩ አገራዊና የጋራ ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ አባላቱን በማሳተፍ እንቅስቃሴ እያደረገ እንደሚገኝ የወቅቱ የማህበሩ አስተባባሪ ዶ/ር ንጉሴ ጣፋ ገልጸዋል፡፡ የማህበሩን አመራር የማጠናከርና እንቅሰቃሴውን ይበልጥ አጠናክሮ ለማስቀጠል እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
በወቅቱም ለመድረኩ ተሳታፊዎች የአገራችንን ወቅታዊ ጉዳዮች በዋናነት የሰሜኑ የአገራችን ክፍል ግጭት ስለመቆሙና ጉዳዩን በውይይትና በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት እየተደረጉ ያሉ ጥረቶችን ጨምሮ ሌሎች ተያያዥ ወቅታዊ ጉዳዮች፣ መንግስት በኦሮሚያ ክልል የአሸባሪው ኦነግ ሸኔ ፀረ-ሰላም እንቅስቃሴን ለመግታት እያካሄደ ያለውን የህግ ማስከበር ዘመቻ፣ የአገራችን ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ የሚያስችል አካታች አገራዊ የምክክር መድረክ መቋቋምና እያካሄደ ያለውን እንቅስቃሴ፣ ስለታላቁ የህዳሴው ግድብ የእስካሁን አፈጻጸም፣ የ3ኛው ዙር የውሃ ሙሌት እና የታችኛው አገራት የተለመደው አፍራሽ እንቅስቃሴ፣ የኢትዮጵያና ሱዳን የድንበር ውዝግብና ጉዳዩን በሰላማዊ አግባብ ለመፍታት መንግስት እያደረገ ያለው ትዕግስትና ጥበብ የተሞላበት ዲፕሎማሲዊ ጥረት፣ በአገራችን እየተስተዋለ ያለው የዋጋ ንረትና ንረቱን ለመቀነስ የመንግስት የአጭርና የረጅም ጊዜ የመፍትሄ እርምጃዎች እንዲሁም ሌሎች ተያያዥ ወቅታዊ ጉዳዮችን አስመልከቶ አቶ ሙሉጌታ ዝርዝር ገለጻና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ተሳታፊዎች በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ስለተደረገላቸው ገለጻ በማመስገን ግልጽ እንዲሆንላቸው የሚፈልጉ ጉዳዮች ላይ ጥያቄያቸውን እንዲሁም ከሚኖሩት አገርና በተሰማሩበት የሙያ መስክ ያካበቱትን ልምድና ዕውቀት መነሻ በማድረግ ለአገራችን ሰላምና ልማት እንዲሁም ለዜጎች ደህንነት መረጋገጥ ይጠቅማሉ ያሏቸውን አስተያየቶች በግልጽ ያቀረቡ ሲሆን በቀረቡት ጥያቄዎችና አስተያየቶች ላይ ጠቃሚ ሃሳቦችን በማሸራሸር የጋራ ግንዘቤ መፍጠር ተችሏል፡፡
በተጨማሪም የመድረኩ ተሳታፊዎች አገራዊ ጉዳዮችን በቅርበት እንደሚከታተሉና የበኩላቸውን ተሳትፎ እያደረጉ መሆኑን በመጥቀስ፤ ስለአገራችን ወቅታዊ ሁኔታ በመደበኛነት ቨርቹዋል መድረክ እንዲፈጠርላቸው፣ ለአገራዊ ጥሪ አቅም በፈቀደ መጠን የሙያ፣ የሞራልና የገንዘብ ድጋፎችን አጠናክው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል፡፡ በቅርቡም ኤምባሲውና ማህበሩ በሚያመቻቹት የጋራ መድረክ የታላቁ ህዳሴ የቦንድ ግዥን ጨምሮ ሌሎች ተሳትፎዎችን ለማድረግ ዝግጁነታቸውን አረጋግጠዋል።
በክብር ቆንስልና በኮሙኒቲው ማህበር ያለው የስራ ግንኙነትና ቅንጅት እንዲብራራላቸው በጠየቁት መሰረት ማብራሪያ አግኝተዋል፡፡ የተጉዋደሉ የማህበሩ አመራሮች የማሙዋላትና የማጠናከር እንዲሁም የማህበሩን የምዝገባ ፈቃድ በማሳደስ የተጠናከረ እንቅስቃሴ ማድረግ እንደሚገባ ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡
በአገሪቱ የሚገኙ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አባላት በናሚቢያ ቆይታቸው ከኤምባሲው የሚያገኟቸውን የተለያዩ የቆንስላና የኢሚግሬሽን አገልግሎቶች ኤምባሲው በናሚቢያ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የክብር ቆንስልና ከማህበሩ ጋር በመቀናጀት አገልግሎቶቹ ይበልጥ ፈጣንና ቀልጣፋ ለማድረግ እንደሚሰራም ተገልጾላቸዋል፡፡
በናሚቢያ በአጠቃላይ ከ250 እስከ 300 የሚጠጉ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አባላት በተለያዩ ከፍተኛ የሙያ መስኮች በመንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተቀጥረው አገራችንንና ህዝባችንን በሚያኮራ ሙያዊ ብቃትና መልካም ስነምግባር በመታገዝ በማገልገል ላይ ይገኛሉ፡፡
በፕሪቶሪያ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ኤምባሲ