48ኛው የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስት (ኢጋድ) የሚኒስቴሮች ምክርቤት መደበኛ ስብሰባ በሱዳን ካርቱም በመካሄድ ላይ ይገኛል።
በመክፈቻ መርሀግብር ላይ ንግግር ያደረጉት የኢጋድ ዋና ፀሃፊ ክቡር ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ ኢጋድ በቀጠናው ሰላምና መረጋጋት እንዲረጋገጥ አዎንታዊ ሚና እየተጫወተ እንደሆነ የጠቀሱ ሲሆን በቅርብ በኢትዮጵያ የተደረሰው የሰላም ስምምነትም የዚያ ማሳያ መሆኑን ጠቁመዋል።
ዋና ፀሀፊው ኢጋድ ከዚህ በተጨማሪም የአየር ንብረት ለውጥን፣ ድርቅን፣ ተባይ እና ወቅታዊ የጎርፍ አደጋዎችን ለመከላከል እንዲሁም ለምግብ ዋስትና ያለውን ተግዳሮት ለመቅረፍ ምላሽ ለመስጠት ከአባል ሀገራት ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑንም አብራርተዋል።
 
ስብሰባውን እየተካፈሉ የሚገኙት የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ክቡር አቶ ደመቀ መኮንን በበኩላቸው የሰላምና ፀጥታ ጉዳይ ለቀጠናው ትልቅ ፋይዳ እንዳለው አፅንኦት ሰጥተው የተናገሩ ሲሆን ኢትዮጵያ ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ በነበረችበት ወቅት የኢጋድ አባል አገራት የሰጡት ያልተቋረጠ ድጋፍ በኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ ምስጋና የሚያሰጠው ተግባር መሆኑን ተናግረዋል።
አክለውም በሰሜኑ ኢትዮጵያ ክፍል የነበረውን ግጭት የኢትዮጵያን የግዛት አንድነት እና ሉዓላዊ ክብር ሙሉ በሙሉ ባከበረ መልኩ እንዲፈታ ከስምምነት መደረሱ በቀጠናው እና ከዚያም በላይ ላሉ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄዎች ስለመኖራቸው ትምህርት ሰጪ አካሄድ መሆኑን ተናግረዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአየር ንብረት ለውጥ እና እያደረሰ ባለው ተፅዕኖ ዙሪያም ያላቸውን ስጋት የገለፁ ሲሆን ይህን ለመግታትም አባል ሀገራት እና አጋሮች የተቀናጀ ጥረት እንዲደረጉ ጠይቀዋል።
የኢጋድ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የቀጠናዊውን ሰላምና ደህንነት፣የሰብአዊነት እጩ ሁኔታን ሪፖርት የሚያዳምጥ ሲሆን በዛሬው እለትም ጋዜጣዊ መግለጫ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።

Disclaimer: The official text of the Embassy Website is the English language version. Any discrepancies or differences created in translations are not binding and have no legal effect for compliance or enforcement purposes.

X
Twitter
Facebook
YouTube
Instagram