በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር የሆኑት ዶ/ር ሙክታር ከድር ከደቡብ አፍሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስትር ክብርት KC Mashego-Dlamini ጋር የሁለትዮሽ ግንኙነትን ስለማጠናከር፣ በአህጉራዊና ዓለማቀፋዊ ጉዳዮች እንዲሁም በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደረገ ጠቃሚ ውይይት አካሂደዋል፡፡
የኢትዮጵያና ደቡብ አፍሪካ ታሪካዊ የወዳጅነት ግንኙነት በጠበቀ አፍሪካዊ ወንድማማችነትና ፓን አፍሪካኒዝም መሰረት ላይ የተገነባ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱም ቀደም ብሎ በታላቁ አድዋ ድል ወቅት ለጸረ አፓርታይድና ጸረ ቅኝ አገዛዝ ንቅናቄ ከተፈጠረው መነሳሳት ጋር ተያይዞ የተጀመረ መሆኑን እ.ኤ.አ. ከ1994 ጀምሮ ደግሞ በዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ተደግፎ በመደበኛነት ተጠናክሮ እየቀጠለ መሆኑን አንስተዋል፡፡
 
ወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ አምባሳደር ዶ/ር ሙክታር ከድር ለክብርት ምክትል ሚኒስትርና ለስራ ባልደረቦቻቸው አስፈላጊ የሆነውን ማብራሪያ በዝርዝር አቅርበዋል፡፡በዚሁም ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ መንግስት ሰላም ወዳድ መሆናችንን፣አሁን የተከሰተው ግጭት ከዚሁ ጽኑ የሰላም ፍላጎት በተቃራኒ የተካሄደ መሆኑን፣ከዚህ ችግር በፍጥነት ለመላቀቅ መንግስት ችግሩ እንዳይከሰት ካደረገው ፈታኝ ጥረት በተጨማሪ በርካታ እርምጃዎችን እንደወሰደ፣ ዕርዳታ ለሚፈለጉ የትግራይ ዜጎቻችን ያልተገደበ የዕርዳታ አቅርቦት ተግባራዊ መደረጉ፣ የአስቸኳይ ጊዜ ዘዋጁ እንዲነሳ መደረጉ፣ በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት ለሚካሄደው የሰላም ድርድር ተገቢ ትብብር ማድረጉ፣ በክቡር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሚመራ 7 አባላት ያሉት የሰላም ተደራዳሪ ተቋቁሞ ፣ አስገዳጅ ቀጣይነት ያለው የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እንዲደረስ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን ገልጸዋል፡፡
 
በሌላ በኩል ህወሃት ግጭቱ እንዲከሰት፣ እንዲባባስና መፍትሄ እንዳይገኝለት አፍራሽ ሚና መጫወቱን እንደቀጠለ፣ ለዓለማቀፉ ማህበረስብ ሰላም ፈላጊ ሆኖ ለመታየት ቢሞክርም አሁንም አጎራባች የሆኑትን የአማራና የአፋር መሬቶችን በወረራ ይዞ እንደሚገኝ፣ በተለያዩ ግንባሮች ለ3ኛ ጊዜ ጦርነት ከፍቶ እንደሚገኝ፣ ከዓለም የምግብ ድርጅት( WFP) 570 000 ሊትር ነዳጅ ዘርፎ እንደወሰደ፣ ወደ ትግራይ ዕርዳታ ሲያመላልሱ የነበሩ በርካታ ከባድ ተሸከርካሪዎች ቀምቶ ለታጣቂዎች ማጓጓዣ እንዳደረገ፣ መንግስት ያደረጋቸው የሰላም ጥረቶች በሙሉ በህወሃት ምክንያት ውጤት አልባ ሆነው እንደቀሩ አስረድተው አንዳንድ የዓለማቀፉ ማህበረሰብ አካላት ጥፋተኛውን ለይቶ በማያርም ሁኔታ ሁለቱም ወገኖች እያሉ የሚያወጡት መግለጫ ህወሃት በዕኩይ ድርጊቱ እንዲገፋበት የሚያበረታታ መሆኑን በማስረዳት የህወሃትን የሃሰት ትርክት ተቀብለው ሳያጣሩ የሚያሰራጩ ታዋቂ ነን የሚሉ አንዳንድ አካላት አለማቀፉ ማህበረሰብ ዕውነታውን በቅጡ እንዳይረዳ አድርገዋል፡፡ሆኖም ቀስ በቀስ እውነታው እየታወቀ ህወሃት እየተጋለጠ የመጣበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡
 
በኢትዮጵያ መንግስት በኩል ተገዶ የአገር ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነቱን ለማስከበር የመከላከል እርምጃ እየወሰደ ቢሆንም አሁንም ለሰላም የዘረጋው እጅ እንዳልታጠፈ ቁርጠኝነቱም እንደተጠበቀ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ክብርት ምክትል ሚኒስትሯም የደቡብ አፍሪካና የኢትዮጵያ ግንኙነት የጀመረው ከጸረ አፓርታይድ ትግሉ ወቅት ጀምሮ እንደሆነ፣ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቱ ደግሞ እ.ኤ.አ. ከ 1994 ጀምሮ መሆኑን፣ ኢትዮጵያ ለነጻነት ታጋዩ ኔልሰን ማንዴላ የኢትዮጵያ ፓስፖርት አዘጋጅታ በመስጠት፣ እ.ኤ.አ. በ1962 የ3 ወራት ወታደራዊ ስልጠና በአዲስ አበባ በመስጠት እንዲሁም ለነጻነት ታጋዮች ያደረገችው ድጋፍ ደቡብ አፍሪካ ትልቅ እውቅና የምትሰጠው መሆኑን፣ ታላቁ ሰው ኔልሰን ማንዴላም Long Walk to Freedom በሚባለው መጽሃፋቸው ላይ ስለ ኢትዮጵያ ያላቸውን አድናቆት መግለጻቸውን በማብራራት ግንኙነታችን ታሪካዊ መሆኑንና ወደፊት በተለያዩ መስኮች ግንኙነቱን አጠናክሮ ማስቀጠል ትኩረት እንደሚሰጠው ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሰላም መሆን ለአፍሪካ ቀንድና ለአህጉሩ ሰላም ያለውን አወንታዊ ፋይዳ ያነሱት ምክትል ሚኒስትሯ በኢትዮጵያ በቅርቡ እንደገና ያገረሸው ግጭት ደቡብ አፍሪካን እንደሚያሳስባት፣ ግጭቱ ቆሞ ሰላም እንዲሰፍንና ለጉዳዩ በድርድር ላይ የተመሰረተ ፖለቲካዊ መፍትሄ እንዲሰጠው እንደምትፈልግ ገልጸዋል፡፡ መፍትሄውም በአፍሪካ ህብረት ማዕቀፍ እና በህብረቱ የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ክቡር ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ አማካይነት የሚካሄደውን ድርድር ደቡብ አፍሪካ እንደምትደግፍ አረጋግጠዋል፡፡
ደቡብ አፍሪካ ኢትዮጵያ ያጋጠሟትን ችግሮች ለመፍታት የሚያስችል ቁመና ላይ እንደሆነች እንደሚገነዘቡ በመግለጽ ክቡር አምባሳደሩ የተሰጣቸው ታላቅ ተልዕኮ እንዲሳካ እርሳቸው የሚመሩት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መ/ቤት አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል፡፡

Disclaimer: The official text of the Embassy Website is the English language version. Any discrepancies or differences created in translations are not binding and have no legal effect for compliance or enforcement purposes.

X
Twitter
Facebook
YouTube
Instagram